የ25 ተኛ ዓመት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልዕክት

ይህ ቃል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በወዳጁ በክቡር ዳዊት አድሮ የተናገረው ቅዱስ ቃል ነው። ቃሉም ሰምና ወርቅ የሆነ ምሳሌያዊና ምሥጢራዊ
አነጋገር ነው። ከዚህ የጥቅስ ቃል ውስጥ እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፣ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፣ በዕረፍት ውኃ ይመራኛል ያለውን ቃል መጀመርያ
ሰሙን ቀጥሎም ወርቁን እናያለን። በባህላችን እንደምናውቀው እረኛ (ጠባቂ) ማለት የበጐችና የከብቶች ጠባቂ፣ ሰብሳቢ፣ አሰማሪና መጋቢ ነው።
እረኛ በጐቹና ከብቶቹ እንዳይጠፉ፣ እንዳይከሱ፣ ሌባ እንዳይሰርቃቸውና አውሬ እንዳይበላቸው ሌሊትና ቀን ተግቶ ይጠብቃል። የለመለመ ሣርና
ቅጠል ባለበት ቦታ ያሰማራል። ይኽ ሰሙ (ምሳሌው) ሲሆን ወርቁ ደግሞ ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር እንደ መልካም እረኛ ሆኖ ተነግሯል።
ምክንያቱም ዲያብሎስ ሌባ እንዳይሰርቀን ፣ ኀጢአት ረሃብ እንዳያከሳን፣ ለዘለዓለም ያማያስርበውን ምግበ ወንጌልን እንዳንራብ፣ የለመለመች መስክ
ቤተ ክርስቲያንን በየሀገሩ እያሳነፀ፣ በቅዱስ ቃሉ እየሰበሰበ የሚጠብቀን ደጉ እረኛ እግዚእብሔር ነውና።
በመዝሙር 144፦ “አንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ “አንተ በጊዜው የሚያስፈልጋቸውን ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ” ይላል። እግዚአብሔር
ፍጥረታትን ሁሉ በመግቦቱ ይጠብቃል። ይልቁንም ከርሱ በታች የፍጥረታት ገዥ አድርጎ የፈጠረውን ሰው ከትንሽነቱ ጀምሮ በአርአያውና
በምሳሌው ከፈጠረ በኋላ በልጅነት አክብሮ በገነት እንዲኖር አሰማርቶታል። በኋላም በመረጠውና በሚወደው በንጉሥ ሰሎሞን አድሮ በዕረፍት
ውኃ፣ በለመለመ መስክ የተመሰለውን ቤተ መቅደስ አሠርቶ ሕዝበ እሥራኤል መንጋውን አሰማርቷል። ቀጥሎም ነቢያትን፣ ሐዋርያትንና መምህራንን
እያስነሳ በጐች የተባሉ ምዕመናንን ጠብቋል።
ከዚህ እንደተገለጸው የእረኞች አለቃ እግዚአብሔር በጐች ምዕመናንን የሚያሰማራበት በለመለመች መስክ በዕረፍት ውኃ የተመሰለች ቅድስት ቤተ
ክርስቲያን ታስፈልጋለች። የእግዚአብሔር መንጋ (መንጐች)፡ለሆኑት ለክርስቲያኖች በሚኖሩበት ሀገር ሁሉ አምላክን የሚያመልኩበት፣ መሥዋዕት
የሚያቀርቡበት፣ ጸሎት የሚጸልዩበት፣ ምስጋና የሚያቀርቡበት፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት፣ ምግበ ወንጌልን የሚመገቡበት፣
በአጠቃላይ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚያካሂዱበት ሐዋርያዊትና ክርስቶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሊኖራቸው ግዴታ ይገባል። ክቡር ዳዊት
በመዝሙሩ በዕረፍት ውኃ መስሎ በም ሥጢር የተነበየላት ቤተ ክርስ ቲያን ናት።
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስና በሐዋርያት የተተኩ የረቀቀውንና የገዘፈውን ምሥጢረ እግዚአብሔር ለበጐች ምዕመናን
የሚያስተምሩ፣ በሰማይና በምድር ማሰርና መፍታት የሚችሉ የእግዚአብሔር እንደራሴዎች መምህራንና ካህናት መኖርም ወሳኝ ነገር ነው።
ምክንያቱም ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ በማቴ 16፡18-19 “በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ ፣ የገሀነም ደጆችም አይችሏትም፣ የመንግሥተ
ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ፣ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል””
ብሏል። በዮሐንስም ምዕ. 21፡15-17 ላይም “ግልገሎቼን አሰማራ፣… ጠቦቶቼን ጠብቅ፣… በጐቼን አሰማራ” እንዳለው ይታወቃል። ግልገሎቼን ያለው
ሕፃናትን፣ ጠቦቶቼን ያለው ወጣቶችን፣ በጐቼን ያለው አባቶችንና እናቶች ምዕመናንን ነው። በተለይም በባዕድ ሀገር ወይም በስደት ሀገር ለሚገኙ
ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያንና እረኞች ካህናት እንደ አባት፣ እንደ እናት፣ እንደ ወንድም፣ እንደ እኅት፣ እንደ ዘመድና ሀገር ናቸው።
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር የጸጋው ግምጃ ቤት ናት። በውስጧ የሚታይና የማይታይ ብዙ ጸጋዎች አሏት። የማይታየውን ጸጋዋን ለማየት
የሚቻለው በንጹሕ እምነትና ዕውቀት ብቻ ነው። ለምሳሌ ራሱ እግዚአብሔር ረቂቅ ስለሆነ በእምነት እንጂ በዐይነ ሥጋ አይታይም። በደላችን
በንስሐና በካህኑ ክህነት ሲሰረይልን በዐይን አይታይም። የቤተ ክርስቲያን መሪዋና ኃላፊዋ ክርስቶስ ስለሆነ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት፣ ጸጋና በረከት
አላት። ይህንን የእግዚአብሔር ጸጋ ለምዕመናን የሚያከፋፍሉ እርሱ የሾማቸው ካህናት ናቸው።
የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በዚህ በሰሜን አሜሪካ በዋሺንግተን ዲሲ በ1985 ዓመተ ምሕረት ከተመሠረተች ጀምሮ በልዩ ልዩ
ፈተናና ችግር ምክንያት የሚወዷትን ሀገራቸውን ኢትዮጵያን ትተው የመጡ ኢትዮጵያውያንን በባዕድ ሀገር ተበትነው እንዳይቀሩ፣ ሃይማኖታቸው
እንዳይጠፋ በማድረግ ትልቅ ገድል ፈጽማለች። ስለዚህ የሃያ አምስተኛ ዓመት በዓሏን ስታከብር ታላቅ መንፈሳዊ ደስታ ይሰማታል። ካቴድራላችን
ያለፈውንና አሁን ያለውን የታሪክ ጉዞዋን በበዓሏ ምክንያት በአጭር በአጭሩ ታወሳናለች። መቼም የዚህችን ቤተ ክርሰቲያን ታሪክ ስናነሳ እንደ
ሐውልት ጐልቶ የሚታየው የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መሥራችነትና አገልግሎት ነው። ከእርሳቸውም ጋር የሊቀ ትጉሃን ፍቅሬ እና የሌሎችም ካህናት
አገልግሎት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ከእኔ የአገልግሎት ዘመን በፊት የነበረው ጉዞ በሌሎችና በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሊገለጽ ይችላል። በእኔ በኩል ግን ለሁለት ዓመት በአገልጋይ ካህንነት፤
ለአሥራ ሦስት ዓመት ተኩል በአስተዳዳሪነት ከተመደብኩበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የቤተ ክርስቲያን ጉዞ በአጭሩ ለመጠቆም እሞክራለሁ። በአንድና
በሁለት ካህናት ትገለገል የነበረች ቤተ ክርሰቲያን መደበኛና ኢመደበኛ በሆኑ ከሃያ በላይ በሚበዙ ካህናት እየተገለገለች ነው። የደብራችን ሰንበት
ትምህርት ቤት መዘምራንም ከመብዛታቸውና አገልግሎት ከመስጠታቸውም በላይ በአስተዳደር ውስጥ እየገቡ ቤተ ክርስቲያንን በመምራት ላይ
ይገኛሉ። ይህ ትልቅ እድገት ነው። ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸው እዚህ የተወለዱ ልጆች ከሃምሳ አይበልጡም ነበር። አሁን ከሁለት መቶ
ሰማንያ የሚበዙ ልጆች ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠውን ትምህርት እየተማሩ ነው። በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ተተኪ ትውልድ እያደረሰች ነው።
5
የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል 25ኛ የብር ኢዮቤል ዩ
በተጨማሪም ወደፊት በእንግሊዘኛና በአማርኛ የሚያስተምሩ፣ የሚቀድሱ፣ የሚጸልዩና የሚመክሩ ከአሥራ አምስት የሚበዙ ዲያቆናትንም
አውጥታለች። ምዕመናንም ቢሆኑ ከድሮው ይልቅ አብዛኛዎቹ ንስሐ የገቡና የቆረቡ ናቸው። የቤተ ክርስቲያን ዋናው ዓላማ ሰውን ወደ ንስሐ
ሕይወት ማምጣት ነው። ለዚህ ያልበቁትም እየተዘጋጁ ነው። የካህናት አገልግሎት በማኅሌት፣ በሰዓታት፣ በቅዳሴ፣ በጸሎትና በሁሉም አገልግሎት
በእጥፍ ጨምሯል። በልማትም ቢሆን አለ የተባለ መንበር ከኢትዮጵያ አስመጥታለች፣ ግርማ ያለው መቅደስ አሠርታለች፣ ያላለቀውን የአዳራሽ
ጣርያና ግድግዳ፣ ወለሉንም ጭምር ሠርታለች፤ ለሃያ ዓመታት ያገለገለ የቤተ ክርስቲያኑን ወንበር ቀይራለች፤ ሌሎችም ብዙ እድሳቶች ተከናውነዋል፤
ከምንም በላይ የሆነውን ሰላምን በመጠበቅ በአንድ ወቅት የነበረው የሰላም ማጣት ችግር በዕርቅ ከተፈታ በኋላ ቤተ ክርስቲያናችን ለረጅም ጊዜ
በቅዱስ ሚካኤል ጥበቃና በአገልጋዮቿ ጸሎትና ጥረት ከማንኛውም ጊዜ የተሻለ ሰላም አላት። በአጠቃላይ እረኛችን እግዚአብሔር በቤተ ክርሰቲያን
ጥላ ሥር ሰብስቦ እየጠበቀን ነው። የእግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን።