የ25ተኛ ዓመት የሰበካ ጉባኤው (የቦርዱ) አስተዳደር መልዕክት

ከሁሉ አስ ቀድሜ ሃይማኖቱንና ሀገሩን ከማ ይረሳው ትውልድ ተቆጥረን የቤተ ክርስ ቲያናችንን ምሥረታ 25ኛ ዓመት ኢዮቤል ዩ መ ታሰቢያ በዓል
ለማክበር በመብቃታችን በራሴና ዛሬ እያገለገለ በሚገኘው የሰበካ ጉባኤ (ቦርድ) አስተዳደር ስም ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋናችንን አቀርባለሁ::
ካህናቱንና ሕዝቡን በፍቅርና በሕብረት ጠብቆ ለዚህ ታላቅ ቀን እንዳደረሰን ሁሉ እንዲሁ ባርኮና ጠብቆ ለ50ኛው ዓመት እንዲያደርሰን በጸሎት
በልመናና በምልጃ ተግተን እንደየተሰጠን ጸጋና መክሊት ለደብራችን አገልግሎት የተፋጠንን ሆነን እንድንቆይ አምላካችን ያበርታን::
በአሜሪካ ተወልደው ካደጉት በስተቀር እኛ አብዛኞቻችን በሥጋ ከተወለድንባት ሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶችና ችግሮች ወጥተንና በፈቃድ
ለቀንም ስዱዳንና መጻተኞች ሆነን ባልተወለድንበት ሀገር ስንኖር ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል:: ሁላችንም ግን በቤተ ክርስቲያናችን ተገኝተንና
ተገናኝተን የኢትዮጵያ ልጆች ቅዳሴውን አስቀድሰን ዝማሬውን ሰምተንና ስብከተ ወንጌሉን ተመግበን በባዕድ አገር ስንኖር የክርስቶስ ቤተሰብነት
እንጂ ከቶውንም የመጻተኛነት ስሜት ኖሮን አያውቅም:: በየእሁዱ በየንግሡና በየክብረ በዓሉ ቁጥራችን እየበዛና ግንኙነታችን በመንፈሳዊና
በማኅበራዊ መስኮች እያደገ ሲሄድም የቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት አድጎና በልጽጎ በሰው ሀገር ያለን እስከማይመስለን ድረስ ትንሿን ኢትዮጵያ
የምናይበትና የምናገኝበት ዋና ሥፍራ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ቆይቶአል::
ለሁላችንም ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተ ጀምሮ ለ25 ዓመታት ትንሿን ኢትዮጵያ አግኝተንበት በክርስቶስ አምነን፣
በትምህርተ ወንጌል ጸንተን፣ በነቢያትና በሐዋርያት ትምህርት ታንጸን የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሆነን በክፉም በደጉም ተሳስረን ለነፍሳችንም
ለሥጋችንም ብዙ በረከት፣ ትሩፋትና ብልጽግና ያገኘንበት የተቀደሰ ሥፍራ ነው:: ቀናት ተቆጥረው ዘመን አዝማናት ተብለው የቤተ ክርስቲያናችን
ዕድሜ 25 ዓመት ሞላው ስንል ጊዜው እንዲህ መብረሩ በጣም ይገርማል:: እግዚአብሔር ፈቅዶና ባርኮ ቤተ ክርስቲያኑ ተመሥርቶ በሰጠው
አገልግሎት ብዙዎቻችን ተቀድሰንበታል፣ ተባርከንበታል፣ ተድረንበታል፣ ልጅ ወልደን፣ ክርስትና አስነስተን፣ በጋሪ ገፍተን አሳድገን፣ በአባቶች
ካህናት አቁርበን፣ በዘማርያን የዝማሬ ትምህርት አዘምረን፣ በሕፃናት ክፍል መምህራን ፊደል አስቆጥረን ልጆቻችን አማርኛ ማንበብና መጻፍ
ችለዋል:: በብዙው የተሳካላቸውም ወላጆች በደብሩ ትጉህና ምግባረ-ሠናይ ካህናት እውነተኛ ሐዋርያዊ ትጋት ግዕዝ ተምረው፣ ውዳሴ ማርያም
ደግመው፣ ለዲቁና በቅተው አንዳንዶቹም በቅዳሴ ጣዕመ ዜማቸው ከምድር እስከ አርያም መንፈሳዊ ልቡናችን እንዲያርግ እንዲጓዝ እያደረጉን
ነው::
የዲሲ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች እንደአሁኑ ሳይገጠገጡና የዛሬው የቨራይዘን ሴንተር ሳይገነባ በዋሽንግተን ዲሲ በ8ተኛው ጎዳና በሰ ሜናዊው ምዕራብ
አቅጣጫ ከቀድሞው ስሚዞንያን ሙዚየም ትይዩ በኪራይ ቤዝመንት ውስጥ በቆሞስ አባ መልአኩ ጌታነህ የአሁኑ ብፁዕ አባታችን አባ ፋኑኤል
በቅዳሴያቸውና በትምህርተ ወንጌል ልዩ ችሎታቸው ሲያገለግሉ ነበር ብዙዎች ተስበን በደም ቅሚ ደብር የተገናኘነው:: ደብረ ም ሕረት ቅዱስ
ሚካኤል ደብሬ ብለን የአቅማችንን ገንዘብ እየሰጠንና ሳምንታቱን እየጠበቅን ወራትን እየቆጠርን ዓመታትን አስከትለን በፍቅርና በእውነተኛ
ክርስቶሳዊ ቤተሰብነት እያደግንና እየበዛን ተጉዘናል:: ጥብቅ ትሥሥራችንም በየጊዜው አርኪና ፍሬ-ብዙ ሆኖ በጥቂት ዓመታት የዛሬውን የደብሩን
ህንጻ በመግዛት እያደገ እየጨመረ ለመጣው የክርስቶስ ቤተሰብ፣ የቅዱስ ሚካኤል ወዳጅና ተከታይ ሰፊ አገልግሎት መስጫ ቤተ ክርስቲያንና ርስት
በባዕድ አገር ሊኖረን ችሎአል::
ይህም ሥፍራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕንፃ ማሻሻያ ግንባታና የኢት ኦ/ቤ/ክ መልክ ይዞ እንዲታደስና እንዲሰራ እየተደረገ ሰፊ የመንፈሳዊ አገልግሎት
ከመስጠት አልፎ ለራሳችን ምዕመናንና ለሌሎችም የአካባቢው የእምነቱ ተከታዮች ለሠርግ፣ ለሃዘን፣ ለክርስትና፣ ለምርቃት (ግራጁዌሽን)፣
ለመንፈሳዊ ጉባኤዎችና ለሕፃናት ትምህርት አገልግሎት እየሰጠ ብዙ መንፈሳዊና ማህበራዊ ትሩፋትንና ጥቅሞችን አስገኝቶልናል::
በዚህ ረገድ የአባታችን የቆሞስ አባ መልአኩ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ችሎታ(የአሁኑ ብፁዕ አባታችን አቡነ ፋኑኤል) ለቤተ ክርስቲያኑ ፈጣን
ዕድገትና ከፍታ ቁልፍ ሚና ያላቸው ሲሆን የገንዘቡና የአገልግሎቱ ለጋሾችና ዋና ባለቤቶች የሆኑት ምዕመናን ወደር የሌለው ክርስቲያናዊ ፍቅር፣
እምነትና አንድነት ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ከቅዱስ ሚካኤል ጋር የተሳሰረ የእምነትና የባለቤትነት መንፈስ ውጤትም ነው፡፡ በእነዚህ 25 ዓመታት ሁሉ
በተለያየ ደረጃና መጠን ነጻ ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን ገንዘባቸውንም ጭምር እየሰጡ በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ የቆዩት ሁሉም ምዕመናን
ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በአመራራቸውም በአገልግሎታቸውም ቤተ ክርስቲያኑን በየጊዜው እያደገና እየተስፋፋ እንዲሄድ ብቃት ያላቸውን መንፈሳዊ
አገልጋዮች በመቅጠር፣ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ሥራዎችን በሁሉም ረገድ ውጤታማ በማድረግ ለሰጡት አመራር ምስጋና ይገባቸዋል::
ከላይ የገለጽነው መልካም ሥራ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ደብሩ ፈተና ሲገጥመውም “ወዘሰ አዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን -እስከ
6
የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል 25ኛ የብር ኢዮቤል ዩ
መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል” ማቴ 10፣22 በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት በጽናት ፣ በሽምግልና፣ በይቅርታና በህግ አግባብ የጋራ
መፍትሄ ላይ በማተኮር ካህናቱም ምዕመናኑም ሳይለያዩና ሳይበታተኑ የቅዱስ ሚካኤል ወዳጅነትን አጠናክረው በመያዝ በጊዜ ሂደት ችግሮች
ተፈትተው ዕርቅ ሊወርድ ችሏል:: የሁሉም ወገን በሚስማማበት በመንፈሳዊ አገልግሎት የበላይነት ላይ ትኩረት በመደረጉም እግዚአብሔር ፈቅዶ
ዛሬ ከመቼውም በበለጠ ጊዜ የምእመናን የአንድነትና የሕብረት መንፈስ ሰርጾ ይገኛል::
ይህን የ25ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል የምናከብረውም ባለንበት ሀገርና በቅድስት ሃገራችን ኢትዮጵያ የነበረው ሲኖዶሳዊ ክፍፍል ቀርቶ ወደ
አንድነት ከመጣን በኋላ በመሆኑ ሁላችንም ኦርቶዶክሳውያን እግዚአብሔር ይመስገን ብለን ደስታችንን እንገልጻለን:: በዚህ ረገድ ባለፈው ዓመት
ሐምሌ 16/2010 (ጁላይ 23/2018) የሲኖዶሱ አንድነት ዕርቅ ተካሄዶ ሲፈጸም ለዚህ ታሪካዊ አንድነት ማብሠሪያ ካቴድራላችን ተመርጦ ሐሙስ
ሐምሌ 19/ 2010 (ጁላይ 26/2018) የዕርቁና የአንድነቱ ዝርዝር መግለጫ ለመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እምነት እምነት ተከታዮች
ይፋ ሲደረግ አባቶች ካህናትና ምእመናን በሰበካ ጉባኤያችን አስተባባሪነት በዕለቱ ይህን ታሪካዊ ታላቅ መርሐ ግብር ለማስተናገድ በመቻላችን
ዕድለኞችም ደስተኞችም ነበርን::ዛሬ እያገለገለ የሚገኘው የሰበካ ጉባኤ (ቦርድ) ያከናወናቸው ብዙ ተግባራትና ክንውኖች ቢኖሩም በወደፊቱ
የካቴድራላችን 25 ዓመታት ውስጥ ሊታዩና ሊከናወኑ ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ በቀረን የ2 ዓመት የአገልግሎት ዘመን ጊዜ እግዚአብሔር
ቢረዳን አሁን ካለን ይዞታና አገልግሎት ሻል ያለና ከፍ ያለ እርከን ገንብተን ለማለፍ በብርቱው የምንጥር ይሆናል:: ይህንንም ለጋሾቹና የአገልግሎት
ምንጫችን የሆኑትን ምዕመናን በመተማመን በጋራ በመሥራትና በፍጹም መንፈሳዊ ትሥሥራችን በመጓዝ የምናደርገው ይሆናል:፡ በዝርዝሩም
ሲገለጽ በአባቶች ካህናት፣ በወንድሞች ዲያቆናት፣ በደብሩ መዘም ራን፣ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ነጻ አገል ግሎት በሚሰጡ የል ዩ ልዩ ኮሚቴዎች
አባላትና በራሳቸው ተነሳሽነት ቤተ ክርስቲያንንና ምዕመናንን ከልባቸው ያለገደብ በሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ተሳትፎ በፍጹም ሃይማኖታዊ
ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን እንድንጓዝ ዕቅዶችና የተግባር መርሃ ግብሮችን እያወጣን እንሰራለን::
እግዚአብሔር አምላክ ላለፉት ዓመታት በሰላም በጤና ጠብቆ ለዚህ 25ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ስላደረሰን ስሙ የተመሰገነ ይሁን::
ሁላችንንም እንዲሁ በሰላም በጤና ጠብቆ ለሌላ 25ኛ ዓመት ያብቃን:: ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ይህችንም የምንኖርባትን አሜሪካንን እግዚአብሔር
ይባርክ ይቀድስ እያልኩ በቤተ ክርስቲያናችን የሰበካ ጉባኤ (አስተዳደር ቦርድ) እና በራሴም ስም ለዚህ መጽሔት አንባቢያንና ለመላው የክርስቶስ
ቤተሰቦች ሁሉ እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ እያልኩ ልባዊ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ::

የ25 ተኛ ዓመት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልዕክት

ይህ ቃል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በወዳጁ በክቡር ዳዊት አድሮ የተናገረው ቅዱስ ቃል ነው። ቃሉም ሰምና ወርቅ የሆነ ምሳሌያዊና ምሥጢራዊ
አነጋገር ነው። ከዚህ የጥቅስ ቃል ውስጥ እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፣ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፣ በዕረፍት ውኃ ይመራኛል ያለውን ቃል መጀመርያ
ሰሙን ቀጥሎም ወርቁን እናያለን። በባህላችን እንደምናውቀው እረኛ (ጠባቂ) ማለት የበጐችና የከብቶች ጠባቂ፣ ሰብሳቢ፣ አሰማሪና መጋቢ ነው።
እረኛ በጐቹና ከብቶቹ እንዳይጠፉ፣ እንዳይከሱ፣ ሌባ እንዳይሰርቃቸውና አውሬ እንዳይበላቸው ሌሊትና ቀን ተግቶ ይጠብቃል። የለመለመ ሣርና
ቅጠል ባለበት ቦታ ያሰማራል። ይኽ ሰሙ (ምሳሌው) ሲሆን ወርቁ ደግሞ ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር እንደ መልካም እረኛ ሆኖ ተነግሯል።
ምክንያቱም ዲያብሎስ ሌባ እንዳይሰርቀን ፣ ኀጢአት ረሃብ እንዳያከሳን፣ ለዘለዓለም ያማያስርበውን ምግበ ወንጌልን እንዳንራብ፣ የለመለመች መስክ
ቤተ ክርስቲያንን በየሀገሩ እያሳነፀ፣ በቅዱስ ቃሉ እየሰበሰበ የሚጠብቀን ደጉ እረኛ እግዚእብሔር ነውና።
በመዝሙር 144፦ “አንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ “አንተ በጊዜው የሚያስፈልጋቸውን ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ” ይላል። እግዚአብሔር
ፍጥረታትን ሁሉ በመግቦቱ ይጠብቃል። ይልቁንም ከርሱ በታች የፍጥረታት ገዥ አድርጎ የፈጠረውን ሰው ከትንሽነቱ ጀምሮ በአርአያውና
በምሳሌው ከፈጠረ በኋላ በልጅነት አክብሮ በገነት እንዲኖር አሰማርቶታል። በኋላም በመረጠውና በሚወደው በንጉሥ ሰሎሞን አድሮ በዕረፍት
ውኃ፣ በለመለመ መስክ የተመሰለውን ቤተ መቅደስ አሠርቶ ሕዝበ እሥራኤል መንጋውን አሰማርቷል። ቀጥሎም ነቢያትን፣ ሐዋርያትንና መምህራንን
እያስነሳ በጐች የተባሉ ምዕመናንን ጠብቋል።
ከዚህ እንደተገለጸው የእረኞች አለቃ እግዚአብሔር በጐች ምዕመናንን የሚያሰማራበት በለመለመች መስክ በዕረፍት ውኃ የተመሰለች ቅድስት ቤተ
ክርስቲያን ታስፈልጋለች። የእግዚአብሔር መንጋ (መንጐች)፡ለሆኑት ለክርስቲያኖች በሚኖሩበት ሀገር ሁሉ አምላክን የሚያመልኩበት፣ መሥዋዕት
የሚያቀርቡበት፣ ጸሎት የሚጸልዩበት፣ ምስጋና የሚያቀርቡበት፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት፣ ምግበ ወንጌልን የሚመገቡበት፣
በአጠቃላይ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚያካሂዱበት ሐዋርያዊትና ክርስቶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሊኖራቸው ግዴታ ይገባል። ክቡር ዳዊት
በመዝሙሩ በዕረፍት ውኃ መስሎ በም ሥጢር የተነበየላት ቤተ ክርስ ቲያን ናት።
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስና በሐዋርያት የተተኩ የረቀቀውንና የገዘፈውን ምሥጢረ እግዚአብሔር ለበጐች ምዕመናን
የሚያስተምሩ፣ በሰማይና በምድር ማሰርና መፍታት የሚችሉ የእግዚአብሔር እንደራሴዎች መምህራንና ካህናት መኖርም ወሳኝ ነገር ነው።
ምክንያቱም ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ በማቴ 16፡18-19 “በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ ፣ የገሀነም ደጆችም አይችሏትም፣ የመንግሥተ
ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ፣ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል””
ብሏል። በዮሐንስም ምዕ. 21፡15-17 ላይም “ግልገሎቼን አሰማራ፣… ጠቦቶቼን ጠብቅ፣… በጐቼን አሰማራ” እንዳለው ይታወቃል። ግልገሎቼን ያለው
ሕፃናትን፣ ጠቦቶቼን ያለው ወጣቶችን፣ በጐቼን ያለው አባቶችንና እናቶች ምዕመናንን ነው። በተለይም በባዕድ ሀገር ወይም በስደት ሀገር ለሚገኙ
ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያንና እረኞች ካህናት እንደ አባት፣ እንደ እናት፣ እንደ ወንድም፣ እንደ እኅት፣ እንደ ዘመድና ሀገር ናቸው።
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር የጸጋው ግምጃ ቤት ናት። በውስጧ የሚታይና የማይታይ ብዙ ጸጋዎች አሏት። የማይታየውን ጸጋዋን ለማየት
የሚቻለው በንጹሕ እምነትና ዕውቀት ብቻ ነው። ለምሳሌ ራሱ እግዚአብሔር ረቂቅ ስለሆነ በእምነት እንጂ በዐይነ ሥጋ አይታይም። በደላችን
በንስሐና በካህኑ ክህነት ሲሰረይልን በዐይን አይታይም። የቤተ ክርስቲያን መሪዋና ኃላፊዋ ክርስቶስ ስለሆነ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት፣ ጸጋና በረከት
አላት። ይህንን የእግዚአብሔር ጸጋ ለምዕመናን የሚያከፋፍሉ እርሱ የሾማቸው ካህናት ናቸው።
የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በዚህ በሰሜን አሜሪካ በዋሺንግተን ዲሲ በ1985 ዓመተ ምሕረት ከተመሠረተች ጀምሮ በልዩ ልዩ
ፈተናና ችግር ምክንያት የሚወዷትን ሀገራቸውን ኢትዮጵያን ትተው የመጡ ኢትዮጵያውያንን በባዕድ ሀገር ተበትነው እንዳይቀሩ፣ ሃይማኖታቸው
እንዳይጠፋ በማድረግ ትልቅ ገድል ፈጽማለች። ስለዚህ የሃያ አምስተኛ ዓመት በዓሏን ስታከብር ታላቅ መንፈሳዊ ደስታ ይሰማታል። ካቴድራላችን
ያለፈውንና አሁን ያለውን የታሪክ ጉዞዋን በበዓሏ ምክንያት በአጭር በአጭሩ ታወሳናለች። መቼም የዚህችን ቤተ ክርሰቲያን ታሪክ ስናነሳ እንደ
ሐውልት ጐልቶ የሚታየው የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መሥራችነትና አገልግሎት ነው። ከእርሳቸውም ጋር የሊቀ ትጉሃን ፍቅሬ እና የሌሎችም ካህናት
አገልግሎት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ከእኔ የአገልግሎት ዘመን በፊት የነበረው ጉዞ በሌሎችና በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሊገለጽ ይችላል። በእኔ በኩል ግን ለሁለት ዓመት በአገልጋይ ካህንነት፤
ለአሥራ ሦስት ዓመት ተኩል በአስተዳዳሪነት ከተመደብኩበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የቤተ ክርስቲያን ጉዞ በአጭሩ ለመጠቆም እሞክራለሁ። በአንድና
በሁለት ካህናት ትገለገል የነበረች ቤተ ክርሰቲያን መደበኛና ኢመደበኛ በሆኑ ከሃያ በላይ በሚበዙ ካህናት እየተገለገለች ነው። የደብራችን ሰንበት
ትምህርት ቤት መዘምራንም ከመብዛታቸውና አገልግሎት ከመስጠታቸውም በላይ በአስተዳደር ውስጥ እየገቡ ቤተ ክርስቲያንን በመምራት ላይ
ይገኛሉ። ይህ ትልቅ እድገት ነው። ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸው እዚህ የተወለዱ ልጆች ከሃምሳ አይበልጡም ነበር። አሁን ከሁለት መቶ
ሰማንያ የሚበዙ ልጆች ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠውን ትምህርት እየተማሩ ነው። በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ተተኪ ትውልድ እያደረሰች ነው።
5
የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል 25ኛ የብር ኢዮቤል ዩ
በተጨማሪም ወደፊት በእንግሊዘኛና በአማርኛ የሚያስተምሩ፣ የሚቀድሱ፣ የሚጸልዩና የሚመክሩ ከአሥራ አምስት የሚበዙ ዲያቆናትንም
አውጥታለች። ምዕመናንም ቢሆኑ ከድሮው ይልቅ አብዛኛዎቹ ንስሐ የገቡና የቆረቡ ናቸው። የቤተ ክርስቲያን ዋናው ዓላማ ሰውን ወደ ንስሐ
ሕይወት ማምጣት ነው። ለዚህ ያልበቁትም እየተዘጋጁ ነው። የካህናት አገልግሎት በማኅሌት፣ በሰዓታት፣ በቅዳሴ፣ በጸሎትና በሁሉም አገልግሎት
በእጥፍ ጨምሯል። በልማትም ቢሆን አለ የተባለ መንበር ከኢትዮጵያ አስመጥታለች፣ ግርማ ያለው መቅደስ አሠርታለች፣ ያላለቀውን የአዳራሽ
ጣርያና ግድግዳ፣ ወለሉንም ጭምር ሠርታለች፤ ለሃያ ዓመታት ያገለገለ የቤተ ክርስቲያኑን ወንበር ቀይራለች፤ ሌሎችም ብዙ እድሳቶች ተከናውነዋል፤
ከምንም በላይ የሆነውን ሰላምን በመጠበቅ በአንድ ወቅት የነበረው የሰላም ማጣት ችግር በዕርቅ ከተፈታ በኋላ ቤተ ክርስቲያናችን ለረጅም ጊዜ
በቅዱስ ሚካኤል ጥበቃና በአገልጋዮቿ ጸሎትና ጥረት ከማንኛውም ጊዜ የተሻለ ሰላም አላት። በአጠቃላይ እረኛችን እግዚአብሔር በቤተ ክርሰቲያን
ጥላ ሥር ሰብስቦ እየጠበቀን ነው። የእግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን።

የ25 ተኛ ዓመት የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መልዕክት

ዘመናትን የምትለውጥ አንተ ግን ለዘለዓለሙ የማትለወጥ፣ ቀንና ሌሊትን፣ በጋንና ክረምትን የምታፈራርቅ ጌታ፣ ለደኅንነታችን የመረጥሃት
ዓመተምሕረት በቅዱስ ወንጌል ስ ላወጅክልን እናመሰግንሃለን።
እንኳን ለደብረ ም ሕረት ቅዱስ ሚ ካኤል ካቴድራ ል ሃያአምስተኛ ዓመት የም ሥረታ በዓል አደረሳችሁ።
ውድ ምዕመናን!
የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በዲሲና አካባቢው ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ለሩብ ምዕተ ዓመት አንድም ቀን
የሚሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ሳያቋርጥ በሕያው እግዚአብሔር ቸርነት፣ በደገኛው በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ከዛሬዋ ቀን የደረሰ
አንጋፋ ቤተክርስቲያን ነው።
ይህ ካቴድራል ባሳለፋቸው 25 ዓመታት ለነገይቱ ቤተክርስቲያን ተረካቢ የሆኑ ዲያቆናትን አስተምሮ ለግብረ ድቁና በማብቃት፣ለምዕመናንም
ቤተክርስቲያኒቷ የምትሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎቶች በሙሉ ማለትም ለሕፃናት ሥርዓተ ጥምቀትን በማከናወን፣በሥርዓተ ተክሊል በቁርባን
በማጋባት፣ ንስሐ በመስጠት ለቅዱስ ቁርባን በማቅረብ፣ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዪትንም በጸሎተ ፍትሐት በመሸኘት ከፍተኛ አገልግሎት የሰጠና፣
እየሰጠም የሚገኝ ቤተክርስቲያን ነው።
በይበልጥም በውጪው ዓለም አንድን ልጅ አስተምሮ ለግብረ ድቁና ማብቃት ብዙ ልፋትን የሚጠይቅና
ታላቅ አገልግሎት ሲሆን በዚህ አገልግሎት የደከሙና የሚደክሙትን ካህናት ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል።
የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜ የሚፈጠሩ ችግሮ ችና ፈተናዎችን ጸሎ ትና ምህላ በመያዝ፣ እርዳታ
ለሚያስፈልጋቸው ገንዘብ አዋጥቶ በመርዳት፣ በተለይም የቤተክርስቲያን ዓይን የሆኑትን ገዳማትና መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ የሆኑትን የአብነት
ትምህርት ቤቶችን ድጋፍ በማድረግ ፣ በአሜሪካም ሆነ በሀገራችን ለሚገኙ ነዳያንን በማብላት ምግብና አልባሳት ቁሳቁሶችንም በማቅረብ
የኃይማኖት ግዴታዋን ስትወጣ ኖራለች።
[ ] እኔ በዚህ ቤተክርስቲያን በቁምስና ሳገለግል ከማልዘነጋቸው የእግዚአብሔር ቸርነቶች አንዱ እንደ ዛሬው በአካባቢውም ሆነ በሀገሩ ካህናት
ባልበዙበት ወቅት አንድም እሁድ እንኳን በሕመምም ሆነ በሌላ እክል የሰንበት አገልግሎቱ ተስጓጉሎ አያውቅም። ጉንፋን እንኳን ቢይዘኝ
እሁድን አሳልፎ በሚቀጥለው ቀን ሰኞ ነበር የሚያመኝ።ይህ የሰው ጥበብ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ የመልአኩም ተራዳይነት ስለነበር ዘወትር
በመገረምና በመደነቅ አምላኬን አመሰግን ነበር።
ዛሬ ይህ የደብረ ም ሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል
ጸጋው የበዛላቸው ብዙ አገልጋይ ካህናት፣ትጉኀን ምዕመናን ፣በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች አገልግሎቱን በስፋት እየሰጠ ይገኛል።
በተጨማሪም የዋሸንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ሆኖ በማገልገልም ላይ ይገኛል።
ይህ ሁሉ በፍቅር መሠረትነት ተመስርቶ በፈቃደ እግዚአብሔር የበረከት ቦታ ለመሆን በቅቷል።ወደፊትም ከዚህ በላይ ብዙ ሥራዎች እንደሚሰራ
እናምናለን።
በመጨረሻም በባዕድ ሀገር በአንድም በሌላ ምክንያት አገናኝቶ ፣በተዋህዶ ጥላ በቤቱ ሰብስቦ፣ ዮሴፍን በስደት የረዳና ያበዛ እግዚአብሔር እኛንም
ረድቶን የቤተክርስቲያናችንን ምስረታ 25ኛ ዓመት ለማክበር በሕይወትና በጤና ስላደረሰን ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር ክብር ምስጋና
ይግባው።
ለደብሩ ካህናት ፣ምዕመናን ረጅም እድሜና ጤና እየተመኘው፣የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት ፣ የመላእኩ የቅዱስ ሚካኤል
ጥበቃና ረድኤት አይለየን አሜን።
አባ ፋኑኤል
የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ!

የቤተ ክርስቲያን ዕርቀ ሰላም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውንና ከ፪፭ ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን መለያየት ለመፍታት በዋሽንግተን ዲስ የተገኙ አባቶች ዕርቀ ሰላሙን በስኬት መከናወን በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሲያውጁ።

2011 የትንሳኤ በዓል

በካቴድራላችን ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የዲሲ እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከፍሯል።